የዘላቂ ኢነርጂ ልማት ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ምክክር ተካሄደ።

የዘላቂ ኢነርጂ ልማት ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ምክክር ተካሄደ። ታህሳስ 25፣ 2015 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር በኢነርጂ ልማት ዘርፍ በተዘጋጀው ዘላቂ የኢነርጂ ልማት ረቂቅ ስትራቴጂ ዙሪያ ምክክር ተደረገ። የምክክር መድረኩን የከፈቱት በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቱ ኢነርጂ ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው በሀገራችን አስተማማኝ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ እንዲሁም የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማትን በበቂ ሁኔታ የሚደግፍ የዘመናዊ ኢነርጂ አቅርቦት መሰረተ ልማትና አገልግሎት በሚፈለግበት ስፍራና ግዜ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክንያት የኢነርጂ አቅርቦት እጥረት እንደሚስተዋል አብራርተዋል። አክለውም የሀገሪቱ የዘመናዊ ኢነርጂ ድርሻ ውስንነት እንዳለበትና እየቀረበ ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ከ48 ከመቶ ያልዘለለ መሆኑን አስታውቀው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነቱ እመርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግና ፍትሃዊነቱን ማረጋገጥ የዘርፉ አንዱ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አመላክተዋል ፡፡ አማካሪው እንደገለጹት አገራችን እምቅ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን ከዚህ ሀብቷ የራሷን የኢነርጂ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ቀጠናዊ የኃይል ትስስሩን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ለማሳደግ እንዲሁም ዘርፉ በአካባቢው ጂኦፖለቲካዊ መረጋጋት ላይ የሚኖረውን ከፍተኛ ሚና ገልጸው በአሁኑ ጊዜ አዋጭ የሆኑ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ እና ከግሪድ ውጭ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በግል ባለሃብቶች፤ የህብረት ሥራ ማህበራት እና በከተማ አስተዳደሮች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ፡ አሰራር እና አደረጃጀት ማሻሻል የሚያሳልጥ አዲስ ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊነትን አስምረውበታል፡፡ አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢነርጂው ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆነ ሀገራዊ የዘላቂ ኢነርጂ ልማት እስተራቴጂ ሲጠናቀቅ የኃይል አቅርቦትን በዘላቂነት ለማሻሻል፣ የኃይል ምርት የአጠቃቀም እና ተስማሚ የኃይል ምንጮች ለማስፋፋት አማራጭ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ገልጸው ረቂቅ ስትራቴጅው ላይ በመወያየት ተጨማሪ ግብአት እንደሚገኝበት አስታውሰዋል። የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ካሌብ ታደሰ በበኩላቸው በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ በትጋት በመሳተፍ ለረቂቅ ስትራቴጂው አስፈላጊውን ግብአት በመስጠት ከስራ ኃላፊነታችን ባሻገር የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡ ዘላቂ የኢነርጂ ልማት ረቂቅ ስትራቴጂው በሚንስትር መስሪያ ቤቱ አነሳሽነት በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ዘላቂ ዘመናዊና ንጹህ ኢነርጂ አማራጮች ላይ መሰረት አድርጎ የሁሉንም ኢነርጂ ተጠቃሚ፤ በተለይ መኖሪያ ቤት፣ ግብርና፣ ትራንስፓርት፣ ኢንዱስትሪ ዘርፎች የኢነርጂ አማራጮችን ማዳረስ ላይ መሠረት ያደረገ ስትራቴጂ ነው፡፡ ረቂቅ ሰነዱ ከዚህ በፊት የነበረው ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም አለም አቀፍ ኢነርጂ ስትራቴጅዎችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኢነርጂ ተደራሽነት ላይ አንዱ ተግዳሮት ኃይልን በቁጠባ መጠቀም ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ ስትራቴጂ ዝግጅት መሠረታዊ የኢነርጂ ችግሮች በመፍታት ፍትሀዊና ዘላቂ የሀይል አጠቃቀምን በማስፈን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚደግፍ ተጠቁሟል፡፡ የምክክር መድረኩ ላይ የዘርፉ የፌደራል የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የክልል የኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎች፤ እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Share this Post