የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ተካሄደ፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ተካሄደ፡፡ ታህሳስ 2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሚያከናውናቸው ተግባራትን ያግዛሉ ተብሎ ለታመነባቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካሪዎች፣መካከለኛ አመራሮች፣ለውሃ ፈንድ አዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በአዳማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡ በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ አማካሪ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ የመድረኩ ዋና ዓላማ የውሃ ልማት ፈንድ ከተቋቋመበት 1994 ዓ.ም ጀምሮ በከተሞች የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የብድር ፋይናንስ በማመቻቸት የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው አሁንም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጃ ተደራጅቶ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ከሌሎች የስራ ክፍሎች ጋር በጋራ ለመስራትና በየዘርፋችን የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ በውሃና ኢነርጂ የውሃ ልማት ፈንድ ተወካይ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዳምጠው ምትኩ በበኩላቸው የውሃ ልማት ፈንድ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የብድር ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው የመድረኩ ዋና ዓላማ የውሃ ልማት ፈንድ የሚያከናውናቸውን ከብድር አሰጣጥ፣ ከብድር አመላለስ እና ከፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ጋር ተያይዞ ምን እየተሰራ እንዳለ ምንስ ክፍቶችና ችግሮች አሉ የሚለውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየደረጃው ያሉ አካላት እውቅናው ኖሯቸው እገዛና አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ታስቦ ነው ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ዳምጠው ገለጻ በሚያከናውኗቸው ተግባራት በርካታ ችግሮች በተለይም ከብድር አመላለስ ጋር ተያይዞ በወቅቱ ማስለመስ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቅሰው እነዚህን ችግሮች መሪ ስራ አስፈጻሚው ብቻውን ሊፈታቸው እንደማይችልና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ በአመራር ደረጃ ያሉና የስራ ክፍሎች ጉዳዩን ተረድተው እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ብድር ለመስጠት የከተሞች መምረጫ መስፈርት፣ የፕሮጀክት አዋጭነት፣ የስራ ማንዋሎች፣ የፕሮጀክቶች አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ የፈንዱ የፋይናንስ ምንጮች፣ የመሪ ስራ አስፈፃሚው መሰረታዊ የብድር አሰጣጥ እና አመላለስ መመሪያ ዙሪያ ግንዛቤ የተሰጠ ሲሆን የውሃ ልማት ፈንድ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 52 ከተሞች ላይ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው እና ሌሎች ከተሞች ላይም ፕሮጀክቶቹ በግንባታ ላይ እንዳሉም እውቅና ተፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በታቀደው ጊዜና ወቅት ብድር መሰብሰብ አለመቻሉ ልማቱን ለሌሎች ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት እንደፈጠረ፣ ክልሎች ለብድር ያላቸው ትኩረት አናሳ መሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የገንዘብ እጥረት፣ ብድር አመላለስ ላይ የህግ ማእቀፍ አለመኖር የሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ እንቅፋት መፍጠሩ በቀረቡ ጽሁፎች ተብራርቷል፡፡ ከተሳታፊዎቹ በርካታ ሃሳብና አስተያየቶች ተነስተው የእለቱን የውይይት መድረክ በመሩት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በተሳታፊዎች ተጎብኝቷል፡፡

Share this Post