ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ለጎረቤት ሀገራት ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ እንዳለ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ለጎረቤት ሀገራት ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ እንዳለ ተገለጸ። ታህሳስ 7/2015ዐዓም(ውኢሚ) ሰባተኛው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሸን ፎረም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ። በፎረሙ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንዳሉት ፎረሙ ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ያጋጠሙ ችግሮችን መነሻ ለመለየት በተደረገው ሂደት እንደተቋቋመ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕላት ፎርም ላይ መሰረት ተደርጎ መካሄዱ ደግሞ ስለ ውሃ ሀብታችን በጥናት ላይ የተመሰረተና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገር የምንችልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለውጥ እንደሚመጣ በማሰብ ነው ብለዋል። በፎረሙ ጅማሮ ወቅት የተደረጉት አራት ፎረሞች በምስረታው ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውና አሁን ላይ እያካሄድን ያለው የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚቀርቡበትና ሳይንሳዊ አስተያቶች የሚገኙበት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የፎረሙ ዋና አላማም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ ተጠቅማ ጎረቤት ሀገራትም ጭምር ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ እንዳለ ለአለም ማህበረሰብ የምናሳውቅበት ነው ብለዋል። በተለያዩ ጊዜያት በተለይም በምእራቡ አለም ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ስራዎች የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን የሚጎዳ አስመስሎ የማቅረቡን ሁኔታ የሚያራግቡ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው በመንግስት ደረጃ የሚሰራው እንዳለ ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎች አለም በሚግባባበት ደረጃና ልክ ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሸ በማድረግ አለም እንዲረዳ በተለይም የሳይንሱ ዓለም እንዲገነዘብና እንዲመረምር መድረኩ ወሳኝነት አለው ሲሉም ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል። ባለፉት አመታት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ሲፈታተናት የነበረው የተዛባ አረዳድ አሁን ላይ በርካታ አገሮች እውነታውን እንዲረዱ በመሰራቱ ግድቡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም መሆኑን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሙያተኞችና የሚዲያ ሰዎች የመሰከሩትና እውነታውን በተለያዩ ሚዲያዎች የዘገቡበት አግባብ እንዳለም ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የውሃ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አካላትን እና የኢትዮጲያ ወዳጆችን እና ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለአለም ለማሳወቅ የሚረዱን አካለትን የፎረሙ ተሳታፊ የሚሆኑበትን እድል እናመቻቻለን ሲሉም አስታውቀዋል። በእለቱ በርካታ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፤ ከቀረቡት መካከል፤ የኢትዮጵያ ዲጅታል ዲፕሎማሲ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ላይ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አለም አቀፍ ትብብር ጥምረት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጥምረት እንቅስቃሴ በካናዳ ምን እንደሚመስልና ሌሎች ተያያዠ ጽሁፎች ቀርበው ወይይት ተደርጎባቸዋል።

Share this Post