በማይክሮ ሶፍት ፕሮጀክት ፕላኒንግና በኮቦቱል ቦክስ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በማይክሮ ሶፍት ፕሮጀክት ፕላኒንግና በኮቦቱል ቦክስ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ህዳር /2015 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በፕሮጀክት ኡደት አስተዳደር ምንነት፣ ማይክሮ ሶፍት ፕሮጀክት ፕላኒንግና በኮቦቱል ቦክስ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው። የስልጠናውን መርሀ ግብር በንግግር የከፈቱት በሚ/ር መ/ቤቱ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኦልቀባ ባሼ ስልጠናው እንደ ሚ/ር መ/ቤት በ2015 በጀት ዓመት የታለሙ አላማዎች ከግብ ለማድረስ በዕቅድ አፈፃፀም ወቅት የሚያጋጥሙ የክህሎትና የዕውቀት ክፍተቶችን ለመፍታት በቴክኖሎጂና በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሁሉን አቀፍ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ የሚያግዝ፣ ወቅቱንና ጥራቱ የተጠበቀ ዕቅድና ሪፖርት ለማዘጋጀት፣ የክትትልና ግምገማ ስርዓት ለመዘርጋት፣ የተቋሙን የመረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ ደግፎ ለማደራጀትና ወረቀት አልባ አሠራርን ለማጎልበት እንደሚረዳ ገልፀዋል። አያይዘውም የተቋሙን የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የዳሰሳ ጥናት መረጃ ለመሰብሰብ፣ ለመተንተን፣ የዲጅታል መረጃ አጠቃቀም እና ደህንነቱ የተጠበቀ አሰራርን ለመተግበር የሚያግዝ እንደሆነ ገልፀዋል። በሚኒስቴር መ/ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ አለሙ መንገሻ ስልጠናው የፕሮጀክት ኡደት አስተዳደራችን ምን ይመስላል የሚለውን በማየት ለክልሎችም ሆነ ለክፍሉ ባለሙያዎች አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀው የልማት ፕሮግራም/ፕሮጀክት እንዴት ይዘጋጃል፣ የማይክሮሶፍት ፕሮጀክት ፕላኒንግ እና የኮቦቱል ሶፍትዌር አጠቃቀም ዙሪያ የመረጃ ልውውጥ ስርዓታችንን ለማዘመን የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል። ስልጠናው በሚ/ር መ/ቤቱ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ባለሞያዎች፣የዋሽ ፕሮጀክት ባለሙያዎች፣ ከአዋሽ፣ ከአባይና ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት የዕቅድ ባለሙያዎች፣ የአስሩም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ መስተዳድር የዕቅድ ክፍል ኃላፊዎች የተሳተፉበት ሲሆን ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ስልጠና ነው፡፡

Share this Post