የፀሃይ ሀይል መስኖን ለማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የፀሃይ ሀይል (Solar Energy) መስኖን ለማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ኅዳር 2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የፀሃይ ሀይልን ለመብራትና ለማብሰያነት ከመጠቀም ባለፈ ለግብርናው ዘርፍ መስኖን የማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታዳሽ ሀይል ፕሮጀክትን ለግብርና ዘርፍ ለመስኖ ልማት እንዲውል በሀገሪቱ 4 ክልሎች በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በሚገኙና በተመረጡ 9 ሳይቶች ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡በዚህም መሰረት ከሰሞኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በደቡብ፣ በሲዳማና በኦሮሚያ ክልሎች ተዘዋውረው የፕሮጀክቱን መጀመር አስመልከቶ ከየቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው በውይይቱ እንዳሉትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ የብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በማስተዋወቅ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ እና አሁን የተጀመረው አዲሱ ፓይለት ፕሮጀክት (DREAM) ማለትም ከፀሀይ ብርሀን የሚገኘውን ኢነርጂ ለመብራትና ለማብሰያነት ከመጠቀም ባለፈ የከርሰምድርና ገጸ ምድር ውሃን በሶላር ፓምፕ አማካኝነት ለመስኖ አገልግሎት በማዋል የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ፕሮግራሙ እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ጉብኘት በተደረገባቸው አካባቢዎች ከሰባት ሺ በላይ የሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የመብራት አገልሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ከ1,200 ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በመስኖ እንደሚለማ ገልጸው የፕሮጀክት ስራው ከGlobal Energy Alliance for people and plant (GEAPP) እንዲሁም ከአፍሪካ ልማት ባንክ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር ዴታው አክለውም ህብረተሰቡ ቃል በገባው መሰረት ፕሮጀክቱ ተጀምሮ አስኪጠናቀቅ ድረስ አሁን ያሳያውን ድጋፍ በሚጠበቅበት ልክ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበው እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤትም ፕሮጀክቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በተዘዋወርንባቸው ቀበሌዎች ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችም አስካሁን መስኖን ሲያለሙ ለ1 ሄክታር መሬት 30 ሊትር ነዳጅ እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ በመሆናቸው የነዳጅ ፍጆታቸውን እንደሚቀንስላቸው፣ የመብራት ተጠቃሚም እንደሚያደርጋቸው እና በዚህም ደስተኞች እንደሆኑ ገልጸው የፕሮጀክት ስራው አስኪጠናቀቅ ድረስ አቅማቸው የፈቀደውን ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡

Share this Post