የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋጭነት ጥናትና ዝርዝር ዲዛይን ፕሮጀክት ውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋጭነት ጥናትና ዝርዝር ዲዛይን ፕሮጀክት ውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡ ህዳር 21/2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የባለብዙ መንደር የአዋጭነት ጥናትና ዝርዝር ዲዛይን ፕሮጀክት ውል ስምምነት ተፈራረመ። ሀረር፣ ሀሮማያ፣ አደሌ፣ አወዳይ ከተሞችና ዋሌምቦ፣ ደንገጎና፣ ሃርላ እና ጀሎቢላ አካበቢዎችን ያካተተ ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የባለብዙ መንደር የአዋጭነትና ጥናትና ዝርዝር ዲዛይን ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራርሟል፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት አካባቢው በርከት ያሉ የመጠጥ ውሃ ችግሮች ያሉበት አካባቢ መሆኑን ገልጸው የኦሮሚያ ክልል፣ የሃረሪ ክልልና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የጋራ ቅንጅት የሚፈልግ ፕሮጀክት ሆኖ የአካባቢውን የመጠጥ ውሀ ችግር ለመፍታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው አያይዘውም ይህንን ጥናት በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ስራውን በታለመለት አጭር ጊዜና የፕሮጀክት በጀት እንደሚያጠናቀው ያላቸውን መተማመን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ሰፊ የክትትልና የድጋፍ ስራ እንደሚያከናውንና የሀረሪ ክልልም የፕሮጀክቱ ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ስራዎችን የመከታተልና ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅበት አውስተዋል፡፡ የአዋጭነት ጥናትና ዝርዝር ዲዛይን ፕሮጀክቱ በ8 ወራት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

Share this Post