የኢትዮጲያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ዓመታዊ አፈፃፀም ተገመገመ ።
ህዳር 13/2015 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) አዲስ አበባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢትዮጲያ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም አፈፃፀም ላይ ከክልልና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ግምገማ ተካሄደ፡፡
ይህ አገራዊ ፕሮጀክት የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም አንዱ አካል ሆኖ እ.ኤ.አ በ2017 የተጀመረና በድጋሚ ተሻሽሎ በ2019 የተተገበረ ሲሆን በ10 ዓመት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ኤሌክትሪክ ማግኘት እንዳለበትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ፕሮጀክት እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ 4 አመታት ያስቆጠረ በመሆኑ መድረኩ ምን ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች የኤሌክትሪፊኬሽን ተጠቃሚ ናቸው የሚለውን ሪፖርት የሚደረግበት፤ ከግሪድ ውጪ በፍጥነት እንዴት ኤሌክትሪክ ያገኛሉ የሚለውን የምናይበት መድረክ መሆኑን እና ሁሉም የገጠር ቀበሌዎችን ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ በኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ላይ የኢትዮጲያ ስታስቲክስ አገልግሎት በአለም ባንክ ድጋፍ የሚደረግባቸውን ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ባቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀምና ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመተንተን ያስቀመጠ ሲሆን በዕቅድ አፈፃፀም ላይ የታዩ ክፍተቶችና የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን በዳሰሰና የእቅድ አፈፃፀማቸውን በመገምገም 3 መቶ ሺ የሚደርሱ ደምበኞችን ለማገናኘት ታቅዶ 91% ተግባራዊ እንደሆነ የኢትዮጲያ ስታስቲክስ አገልግሎት በጥናቱ ጠቁሟል፡፡
የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች 30% ኦፍ ግሪድ ኃይል የሚያገኙ፤ የተቀሩት ከግሪድ የሚያገኙ ናቸው፤ፕሮግራሙን ለማስቀጠል የአለም ባንክ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን በተጨማሪ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡ በኤሌክትሪክና ሶላር ላይ 1 ሚሊዮን የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ከ 700 ሺ የማህበረሰብ ክፍል እየተጠቀመ መሆኑን ተገልጿል፡፡