በኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
በኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡ህዳር 8/2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከዘርፉ ከፍተኛ አመራርች፣ከተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራርች፣ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መካከለኛ አመራርች ጋር በአዳማ ውይይት አካሄደ፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንዳሉት ኢትዮጵያ የ10 ዓመቱን መሪ እቅድ ለማሳካትና ወደ ብልጽግና ጎዳና በምታደርገው ጉዞ የኢነርጂው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና በታዳሽ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ በፖሊሲው አጽንኦት የተሰጠበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም አሁን ባለው ሁኔታ የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ከ47 ፐርሰንት እንደማይበልጥና ይህንን ተደራሽ ያልሆነ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የፖሊሲው አስፈላጊነት የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በፖሊሲው ላይ መወያየቱም ግንዘዛቤን በማዳበር ወደ ተግባር በመቀየር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀድሞ በመረዳት ለትግበራው ስኬታማነት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሰው ረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከአሁን በፊት በርካታ ውይይት የተደረጉበት መሆኑንና ወደ መጨረሻ ምዕራፍ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ እንዳሉትም የኢነርጂ ፖሊሲው ካለፉት 20 ዓመታት በፊት ሲሰራበት የነበረ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ባለው ሁኔታ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ከማህበረሰቡ ፍላጎት ጋር ለማጣጣምና በዘርፉ ማህበረሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ውጤት በሚያመጣ መልኩ ፖሊሲውን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጨምሮ በየደረጃው እስከ ክልል ድረስ ውይይት መደረጉ በፖሊሲው ዙሪያ እውቅና ለመፍጠር ታስቦ እንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡
የፖሊሲው ዓላማም የኢነርጂ ሃብቶችን በፍታህዊነት፤ በዘላቂነትና በአስተማምማኝነት በማልማትና አቅርቦትን በማሳለጥ የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብሎም የሃገር በቀል ኢኮኖሚክ ሪፎርሙንና መዋቅራዊ ለውጡን በመደገፍ ፈጣን ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖር በማስቻል ከኋላ-ቀር ኢነርጂ አጠቃቀምና አቅርቦት ጋር በተያያዘ በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ የጤናና ተያያዥ ችግሮችን በማስወገድ ግዜና ጉልበታቸውን በምርት ሥራ ላይ እንዲያውሉና የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ለማድረግ ነው።
ፖሊሲው የአገራችንን ኢነርጂ ሀብት በፍትሀዊነትና በዘላቂነት አስተማማኝ በሆነ አግባብ በማልማትና አቅርቦቱን በማሳለጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ብሎም የሀገር በቀል የኢኮኖሚክ ሪፎርሙን እና መዋቅራዊ ለውጡን በመደገፍ ፈጣን ብልጽግና እንዲኖር ማስቻል ግብ ላይ የተመሰረተ መሆኑና ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም የኢነርጂ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ አቅም ለማምረት የአገር በቀል ሀብት የገበያ ድርሻን ለማሳደግ፤ እንዲሁም የግል ባለሀብቶችን በዘርፉ መሪ ተዋናይ እንዲሆኑ ማስቻልና በሀይል ስብጥሩ ልዩ ልዩ የታዳሽ ሀይል ማመንጨት እንዲቻል እና ሌሎች አዋጭ የኢነርጂ ምንጮች ለመተካት የፖሊሲውን ትኩረት የሚሻ መሆኑና ሌሎችም ከሴቶች እና ከአካል ጉዳተኞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡