የኢነርጂ መረጃ ተደራሽነት ፕላት ፎርም የስራ ቡድን ለመመስረት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ፡፡

የኢነርጂ መረጃ ተደራሽነት ፕላት ፎርም የስራ ቡድን (Energy Access Explorer Working Group) ለመመስረት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ፡፡ ህዳር 15/2015ዓ.ም (ውኢሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ መረጃ ተደራሽነት ፕላት ፎርም የስራ ቡድን (Energy Access Explorer Working Group) በኢትዮጵያ ለመመስረት የሚያስችል ውይይት በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ተካሄደ፡፡ በውይይቱ መክፈቻ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ርኢ/ር ሱልጣን ወሊ እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የኢነርጂ ፍልጎት እየጨመረ ፣ ጠቀሜታውና ተፈላጊነቱም በዛው ልክ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው የኢነርጂ ዳታ ቤዝ (Energy Access Explorer) በእያንዳንዱ አካባቢ ያለውን የኢነርጂ ምንጭ፣ ፍላጎት እና የት አካባቢም እንዳለ ጭምር መረጃ ማሰባሰብ የሚያስችል ቋት በመሆኑ የሚመለከተው አካል ባለበት ቦታ ሆኖ በቀጥታ መረጃ ማግኘት፣ መተንተን ፣ መጫን ስለሚችል ትክክለኛ የኢነርጂ እቅድ በማቀድ በተፈለገው ልክ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴታው አክለውም የኢነርጂ መረጃ ተደራሽነት ፕላትፎርም (Energy Access Explorer) ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ በኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልግ አካል ሙሉ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ አዋጭነቱን ቀድሞ መረዳት የሚያስችል እድሉ ሰፊ መሆኑንና ለኢነርጂ ብቻም ሳይሆን ለሌሎችም ለውሃ፣ ለግብርና ለጤናና ለመሳሰሉት መጠቀም እንደሚቻል ገልጸው ፕላትፎርሙ በአንዴ ተጠናቆ የሚያልቅ አለመሆኑንና በየጊዜው መረጃ ሲገኝ እየተሻሻለ (Update)እየተደረገ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከአንድ ዓመት በፊት ፕሮግራሙን ለሚመለከታቸው አካላት ማስተዋወቅ የተቻለ መሆኑን ጠቅሰዉ ስራውን በዘላቂነት ለማከናወን ይቻል ዘንድ የስራ ቡድን (Working Group) መመስረት አስፈላጊና የተግባሩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ የስራ ቡድኑ(Working Group) ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከልም በኢነርጂ ዘላቂ ልማት ዙሪያ በባለድርሻ አካላት መካከል አጋርነትን መፍጠርና ማጠናከር፣ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ያሉ አዳዲስ እና ቀጣይ የልማት ውጥኖችን ለመደገፍ የኢነርጂ መረጃ ፕላትፎርም ላይ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን መለየት እና የተጠቃሚዎችን ተሳትፎና ግብረመልስ መከታተል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡:    

Share this Post