ሀገር አቀፍ የአንድ ቋት ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን የፕሮግራም አጋማሽ አፈፃፀም ግምገማ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

ሀገር አቀፍ የአንድ ቋት ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን የፕሮግራም አጋማሽ አፈፃፀም ግምገማ (midterm review) የምክክር መድረክ ተካሄደ። ህዳር 8 ቀን 2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ሀገር አቀፍ የአንድ ቋት የውሃ፣ የሳኒቴሽንና የሃይጂን (One WaSH National Program) የፕሮግራም አጋማሽ አፈፃፀም ግምገማ (midterm review ) የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄደ። የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት የምክክር መድረኩ አላማ ፕሮግራሙን በመተግበር ሂደት ላይ ከአፈፃፀም ጋር ተያይዘው የጋጠሙትን ችግሮች በመለየትና በማረም እንዲሁም በትግበራ ወቅት የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በመጠቀም በቂ የውሃ፣ የሳኒቴሽን እና የሃይጂን አገልግሎት ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው አያይዘው ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ እስከ 2025 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የውሃና ኢነርጂ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በመቀናጀት ፕሮግራሙን የተሻለ አፈፃፀም ደረጃ ማድረስ ያስችላል ብለዋል፡፡ ፕሮግራሙ እስከ እ.ኤ.አ 2019 ዓ.ም. ውጤታማ ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው ነገር ግን በኮቪድ-19፣ በአከባቢው ፀጥታ ችግሮች፣ በጎርፍ እና በተለይም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በፕሮግራሙ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶች አጋጥሟል ብለዋል፡፡ የፕሮግራም አጋማሽ አፈፃፀም ግምገማ (midterm review ) ቀደም ብሎ በአተገባበር ሂደት የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመዳሰስ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ደካማ አፈፃፀሞችን በማረም የተሻለ አፈፃፀም ለማስመስገብ ወሳኝ መሆኑን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልፀዋል፡፡ በመድረኩ በአስር ክልሎች የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን ሥራዎች አፈፃፀም ላይ ሲካሄድ የቆየውን የመስክ ምልከታ ግኝት ሪፖርት ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡ የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀን የሚቆይ ሲሆን የውሃና ኢነርጂ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እና ሀገር አቀፍ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን ማስተባበሪያ ፕሮግራም እና የክልሎች የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን ሰክተር የቢሮ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ከመርሀ ግብሩ መረዳት ተችሏል፡፡

Share this Post