የእንቦጭ አረም ከቆቃ ሀይቅ የማስወገድ ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሃግብር እየተካሄደ ነው፡፡
የእንቦጭ አረም ከቆቃ ሀይቅ የማስወገድ ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሃግብር እየተካሄደ ነው፡፡
መጋቢት 21/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር በቆቃ ግድብ ላይ የተስፋፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የማስጀመሪያ እና የካርታ ርክክብ መርሃ ግብር በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ እንደተቋም "ውሃ ህይወት ነው" የሚል መርህን አንግቦ የሚሰራ በመሆኑ ውሃን ስንጠቀም እንዳይበከልና እንዳይባክን በአግባቡ ልንጠብቀውና ልንንከባከበው እንደሚገባ ገልፀዋል።
አቶ ማሙሻ አያይዘውም የቆቃ ግድብ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀው ሁሉም ዜጋ በጋራ በመሆን የቆቃ ሀይቅን ደህንነት መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ሚሊዮን በቀለ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል ውሀ ቢሮ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ዋነኛው የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃን መንከባከብና መጠበቅ መሆኑን ገልጸው፤ የእንቦጭ አረም የውሃውን ደህንነት ስለሚጎዳ አረሙን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢ/ር ሚሊዮን በቀለ አክለውም ከዚህ በፊት የአካባቢውን ማህበረሰብና ባለሀብቶችን በማሳተፍህ ከደንበል ሀይቅ ላይ አረሙን የማስወገድ ተግባር ውጤታማ መሆኑን ገልፀው፤ ከቆቃ ሀይቅ ላይም እንቦጭን ለማስወገድ የአካባቢው አልሚዎች የተዘጋጀውን ካርታ ተረክበው ሀይቁን ማፅዳትና ዳግም እንዳይከሰት እነደሚንከባከቡት
ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ርክክብ የሚደሰግበት ካርታ በአዋሽ ተፋሰስ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት በቆቃ ሀይቅ በሶስት ክላስተር ላይ የተዘጋጀ ሲሆን በቆቃ ሀይቅ ዙሪያ ለሚገኙ ባለሀብቶችና ውሃ ተጠቃሚዎች የርክክብ መርሀ-ግብር ይካሄዳል፡፡
በመድረኩም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኦሮሚያ ክልል፣ ዞንና ወረዳ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በእንቦጭ አወጋገድ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ፣ ከደንበል ሀይቅ አወጋገድ የተቀመረ ተሞክሮና የቆቃ ሀይቅ ያለበት ሁኔታ እቅድ ቀርቦ በሰፊው ውይይት ይደረጋል።