በኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ፡፡

በኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ፡፡ አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2015 ዓ.ም. በኢትዮጲያ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር በስካይላይት ሆቴል ተካሄደ፡፡ የማስጀመሪያ መርሃግብሩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት በምትዋሰናቸውና ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የከርሰምድር ውሃን በዘላቂነት ለመጠቀምና ተደራሽነትን ለማሳደግና የከርሰምድር ውሃን ለማገገም የሚያስችል ፕሮጀክት አካል መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ የከርሰምድር ውሃን በማስተዳደር እና በትብብር ለመጠቀም እና የታለሙ ማህበረሰቦችን ድርቅን የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን አስታውሰዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም የፕሮጀክቱ ምዕራፍ 1 ሶስቱን ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ሶማሊያን እንደሚያጠቃልል ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከአለም ባንክ በተገኘ 210 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በ55 ወረዳዎች በውሀ አቅርቦት፤ በ67 ወረዳዎች ደግሞ በከርሰምድር ውሃ አለኝታ ጥናት ማድረግ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በ4 ወረዳዎች ላይ የመስኖ ልማት ስራዎችን ለመተግበር ያለመ ነው ፡፡ ፕሮጀክቱ እንደመጀመሪያ በኢትዮጵያ የተለያዩ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የ6 አመት የጊዜ ቆይታ ይኖረዋል። ፕሮጀክቱ በውሃና ኢነርጂ፤በመስኖና ቆላማ አካባቢዎችና በአለም ባንክ ትብብር የሚተገበር ነው። በመርሃግብሩ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኢ/ር አይሻ መሀመድ፣ የወርልድ ባንክ የስራ ሀላፊዎች እና የክልሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

Share this Post