በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መካከል የድርጊት መግባቢያ ስምምነት ተደረገ፡፡
ህዳር 17/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መካከል “ግድቤን በደጄ ኢኒሼቲቭ” ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የድርጊት መግባቢያ ስምምነት ተደረገ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በስነ-ስርዓቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቀጣይ ለምንሰራቸው ስራዎች የድርጊት መግባቢያ ስምምነት ስናደርግግድቤን በደጄ ኢኒሼቲቭ የሚፈጥረውን የስራ እድል መነሻ በማድረግ መሆኑን ገልጸው፤ ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ከተጀመረ 2 አመት የሆነውና ዝናብ አጠርና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት የዝናብ ውሃን ለማሰባሰብ መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል የተሰበሰበውን ውሃ መጠቀም የሚቻልበትን አሰራር የሚተገበርበት መሆኑን ገልጸው፤ በማእከላዊ ጎንደርና በቦረና አካባቢ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱንና “ግድቤን በደጄ ኢኒሼቲቭ” በየአካባቢው በመተግበርና በማላመድ ወጣቶች እንዲሳተፋ በማሰልጠን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ተቋማትም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የውሃ ሽፋንን ለማሳደግ በትኩረት መሰራት እንደሚያስፈልግ አውስተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም የውሃ ጉዳይ የማያገባው ዜጋ እንደሌለ ገልፀው፤ በትምህርት ቤት የምገባ ስነስርአት ሲነሳ የውሃ ጉዳይም አብሮ የሚነሳ በመሆኑ ግድቤን በደጄ ኢኒሸቲቭ ብዙ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ብዙ ተቋማት የውሃ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተደረጉትን የግቢ ማስዋብ ስራ አድንቀው የድርጊት መግባቢያ ስምምነቱ መግባባት ብቻ ሳይሆን ወደተጨባጭ ተግባር ለመግባት ትልቅና ጉልበት የሚፈጥር ሀሳብ በመሆኑ ዜጎችንና ተቋማትን የውሃ ችግራቸውን በመቅረፍ እውቀትና ክህሎት አክለን ቴክኖሎጂውን እንደመልካም አጋጣሚ ወስደን የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት በመስራት እውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በመድረኩ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሃሪ የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ምንነትና በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ውስጥ እየተሰሩ ካሉት ተግባራት መካከል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና በማስፋት ወደተመረጡ 87 አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይ ከመንግስትና ከአጋር አካላት በሚገኘው ድጋፍ አነስተኛ የሶላር ፓምፕ በመጠቀም በተለያየ ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎችን በማደራጀት ወደተግባር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ዶ/ር አቡበከር ካምፖ በሁለቱ ተቋማት የተደረገው ስምምነት ስራአጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎን ሆኖ ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡