የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች እና ሰራተኞች ከተጠሪ ተቋማት ጋር የፀረሙስና ቀንን አከበሩ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች እና ሰራተኞች ከተጠሪ ተቋማት ጋር የፀረሙስና ቀንን አከበሩ፡፡ ህዳር 13 /2016 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች እና ሰራተኞች ከተጠሪ ተቋማት ጋር የፀረሙስና ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ። መርሃግብሩን በንግግር የከፈቱት በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሙስና ለበርካታ ሀገራት ሠላም እና መረጋጋት ለማስከበር አደጋ እየሆና ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ አፀያፊ ተግባር የጥቂቶችን ፍላጎት የሚያሟላ ቢሆንም ብዙሃንን የሚጎዳ እና በሀገር ሀብት ላይ ውድመት የሚያስከትል ብልሹ አሰራር እንደሆነ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አስገንዝበዋል። በሀገር እድገት ላይ የሚያመጣውን አደጋ ለመከላከል ያደጉ ሀገራት ባላቸው ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ለማስቀረት ጥረት ቢያደርጉም አመርቂ ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ የሚኒስትሩ አማካሪ አስረድተዋል። የሚኒስትሩ አማካሪ አያይዘውም ኢትዮጵያ ሙስናን ለመዋጋት አለምአቀፍ የፀረሙስና ስምምነት ቃልኪዳን አባል መሆኗን አስታውሰው፤ ዘንድሮም ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በህብረት እንታገል በሚል መሪ ቃል በአለምአቀፍና እንደሃገር ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን ቀን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የማክበሩን አሰውፈላጊነት አውስተዋል፡፡ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አክለውም እያንዳንዱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ተግባር ተገንዝበው ከሙስና እና ብልሹ ድርጊት ራስን በማራቅ የሙስና አስተሳሰብና ተግባር ሲያጋጥም በቁርጠኝነት እንዲታገሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ። የፌደራል የስነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ወዶ አጦ በበኩላቸው ሙስና በባህሪው እጅግ ውስብስብና ተለዋዋጭ የሆነ ብልሹ አሰራር መሆኑን ገልፀው፣ በብዙሃኑ ፈንታ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት፣ በህዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመንን የሚሸረሽር የአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢካኖሚያዊ ውድመት የሚያስከትል ድንበር ዘለል ወንጀል ነው በማለት አስረድተዋል። በሀገራችንም ሙስናን ለመዋጋት በየደረጃው ያለው አመራሮች እና ሰራተኞች በፀረ ሙስና አውደ ውጊያ በመሰለፍ ከራሱ ጀምሮ ሙስናን መታገል ይጠበቅበታል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ተቋሙም የፀረሙስና ትግሉ በማቀጣጠል ትግሉ እንዲሳካ የአሰራር፣ የአደረጃጀት እና የአቅም ግንባታ አንፃር ምቹ ሁኔታዎችን በመፈጠር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በመጨረሻም በተቋማቱ የተደራጁ የስነምግባር የፀረሙስና ስራ ክፍሎች በግብዓት በመጠናከር በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እና በኢነርጂ ልማት ዘርፎች በተቋሙ ላይ የተጣለውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

Share this Post