የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአምራችነት ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአምራችነት ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ። ጳጉሜ 04/ 2015 ዓ.ም. የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአምራችነት ቀንን የቀድሞ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችንና ሰራተኞች በተገኙበት የተለያዩ ዝግጅቶች በማከናወን አከበረ። ዝግጅቱን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የተቋሙን ታሪካዊ አመሰራረት አስታውሰው መሪዎች በተለያየ ጊዜ ቢቀያየሩም የተቋም ግምባታ ሀገርን እንደሚያስቀጥል ጠቅሰው፤ ክቡር ሚኒስትሩ በዝግጅቱ ላይ ዘርፉ የውሃ ሀብት ክፍል በመባል በስራ ሚኒስቴር ሲቋቋም የስራ ሚንስትር የነበሩትን ራስ መንገሻ ስዩም ጨምሮ፤ ተቋሙን በቅብብሎሽ የመሩት አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ፣ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ፣ አቶ ሞቱማ መቃሳ እና ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለን ለአበረከቱት አስተዋፅኦ ክቡር ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል። የቀድሞ ሚኒስትሮቹም በበኩላቸው በተቋሙ እየታየ ላለው ለውጥ አድናቆታቸውን ገልፀው፤ ለተደረገላቸው የማስታወሻና የምስጋና ፕሮግራም ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋን አመስግነዋል። በእለቱ በተቋሙ የተገነባው ዘመናዊ የዲጂታል ኤግዚቢሽን ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል። በኤግዚብሽኑ መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ክንውኖችን ጨምሮ፤ በሁሉም ዘርፎች ያሉ ጥናቶች በዲጂታል ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መረጃ ለመሰጠት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገልፀዋል። በሌላ በኩል ለ340 ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የተቋሙ ሰራተኞች ለበዓል መዋያ ድጋፍ ተደርጓል።

Share this Post