በብድር የተደገፈ የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት እና የከተሞች መጠጥ ውሃ የብድር ክፍያ ሁኔታ ግምገማ እየተካሄደ ነው።
ግንቦት 09/2015ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ ፕሮግራም በብድር የተደገፈ የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት እና የብድር ክፍያ ሁኔታ ግምገማ እያካሄደ ነው፡፡
መርሀግብሩን በንግግር ያስጀመሩት በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት በሀገራችን ንጹህ የመጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ተደራሽ ማድረግ ጤናማ የሆነ አምራች ዜጋ እንዲኖር ከማገዙም በላይ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማፋጠን ወሳኝ ግብዓትና መሠረተ ልማት መሆኑን አውስተው፤ በዚህም በገጠርና በከተማ እየጨመረ የመጣውን የንጹህ መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ፍላጎት ለማሳደግ የፌደራል መንግስት እና ሌሎች ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በሀገራችን እየተተገበረ ያለው የከተሞች ንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ ከፋይናንስ ድጋፎች በረጅም ጊዜ አነስተኛ ወለድ መልሶ ማበደር ስትራቴጂ ከከተሞች ጋር ውል በመግባት እየሰራ ቢሆንም በውሃ ልማት ፈንድ በኩል ብድር ከወሰዱ ከተሞች ከ50%በላይ በድር መመለስ ባለመቻላቸው ምክንያት ሌሎች ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ለ52 ከተሞችና እና ለ69 ፕሮጀክቶች ተሰጥቶ ከነበረው 1.7 ቢሊየን ብር መመለስ የተቻለው 956 ሚሊየን ብቻ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይ ብድር መመለስ ያልጀመሩ ከተሞች ወደ ክፍያ ስርዓት እንዲገቡ አሳስበዋል ፡፡
በመርሃግብሩ ላይ በዋናነት ብድር ተጠቃሚ የሆኑ በ 52 ከተሞች፣ በአሁኑ ሰአት ግንባታ ሂደት ላይ በሚገኙ 69 የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና ብድር አመላለስ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ይደረጋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ተበዳሪ ከተሞች የሚጠበቅባቸውን የማችንግ ፈንድ ገቢ እንዲያደርጉ፣ በባለ ድርሻ አካላት በኩል የሚታዩ የቅንጂት ችግሮች ቀርፈው ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲያጠናቅቁና ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ላይ የክልል የዘርፉ ስራ አመራሮች፣ የከተማ ውሀ አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች፣ ከፋይናስ፣ ከፕሮጀክት አስተባባሪዎች እና ባለድርሻ አካላት የተገኝተዋል፡፡