በወንጪ ዳንዲ ገበታ ለሀገር የሚገነባ የሙከራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ውል ስምምነት ተደረገ፡

በወንጪ ዳንዲ ገበታ ለሀገር የሚገነባ የሙከራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ውል ስምምነት ተደረገ፡፡ ግንቦት 2/2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዋን ዋሽ ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል ለወንጭ ዳንዲ ገበታ ለሀገር አገልግሎት የሚሰጥ የንጹህ መጠጥ ውሃ የጉድጓድ ቁፋሮና ፍተሻ ስራ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት የውል ስምምነት አደረገ፡፡ የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንዳሉት ይህ የሙከራ ውል የሚገኘውን የውሃ መጠን መነሻ በማድረግ ግምገማ ከተደረተገበት በኋላ ውጤቱን በማየት ሌሎች አራት ተጨማሪ ጉድጓዶች የሚቆፈሩ መሆኑንና የውሃ መስመር የመዘርጋት ስራውም በየደራጀው የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡ የኮንትራት ውል ስምምነቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ 400 ሜትር በ200 ሚሊ ሜትር ስፋት ከተከናወነ በኋላ ስኬታማነቱ ታይቶ እንደ አካባቢው የተፈጥሮ አቀማመጥና ከርሰ ምድር ግኝት መሰረት ጉድጓዶቹ ወደ 254 ሚሊ ሜትር ስፋት የሚያድጉ መሆኑንና ለመጀመሪያው የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደሚደረግበትም ጭምር አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ ክቡር አምባሳደሩ የኦሮሚያ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን በአጭር ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ስራውን አከናውኖ እንደሚያስረክብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እምነት የጣለ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡ የኮንትራት ውል ስምምነቱን የወሰደው የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲሆን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሉ ለማ በኩላቸው ስራውን በተገባው ውል መሰረት በአጭር ጊዜ በጥራት በማከናወን እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል።

Share this Post