በንፁህ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ ላይ በኔዘርላንድ ሄግ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ

በንፁህ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ ላይ በኔዘርላንድ ሄግ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ፡፡ እ.ኤ.አ ከሜይ 02 – 04/2023 በኔዘርላንድ ሄግ ከተማ ከስምንት መቶ በላይ ባለድርሻ አካልትን በማሰባሰብ ‘All Systems Connect’ በሚል መሪ ቃል በንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሸንና ሃይጅን ላይ ያተኮረው የምክክር መድረክ በዘርፉ ላይ ባሉ መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር ሰንብቶ ተጠናቋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የበርካታ ሀገራት የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፤ የለጋሽ ድርጅቶችና የመያድ ተወካዮች፣ የምርምርና ስርፀት ተቋማት፤ የግሉ ዘርፍ ተቋማት፣ የወጣቶችና አንቂ ማህበራት ተጠሪዎች የተገኙበት ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰውን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትንና ድርጅቶችን የወከሉ ከ25 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ የጉባኤው ዋና ዓላማ እ.ኤ.አ ከማርች 22 – 24 በአሜሪካ ኒውዮርክ ሲካሄድ የሰነበተውን የተመድ የውኃ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሃ ግብር እና የዘላቂ ልማት ግቦች ቀሪ ስራዎች ላይ መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እንዲኖሩ ያለመ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ልዑካን በኩል በመድረኩ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባሻገር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በተከታታይ ዓመታት የቀጠለው የድርቅ አደጋ፣ የዋና ዋና የልማት ፕሮግሞች ማስፈጸሚያ የሀብት እጥረት፣የማስፈጸም አቅም ውስንነቶችና በዓለም አቀፍ ገበያ እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረት ጨምሮ እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶች ለጉባዔው አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች ቢያጋጥማትም በመንግስት በኩል የለጋሽ ድርጅቶችን ድጋፍ ከመጠቀም ባሻገር የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቅንጅት እንዲስሩ በማድረግ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ ላይ ውጤታማ ስራ እንዳከናወነች የኢትዮጵያ ልዑካን በጉባዔ ላይ አስረድተዋል፡፡

Share this Post