የሩሲያ የኢነርጂ ካምፓኒ ሩስሀይድሮ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ያለውን ፍላጎት ገለጸ፡፡

የሩሲያ የኢነርጂ ካምፓኒ ሩስሀይድሮ (RusHydro) በኢትዮጵያ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ያለውን ፍላጎት ገለጸ፡፡ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) በሩሲያ ትልቁ የኢነርጂ ካምፓኒ የሆነው ሩስሀይድሮ (RusHydro) በኢትዮጵያ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ያለውን ፍላጎት ገለጸ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የበላይ አመራሮችና የሩስሀይድሮ (RusHydro) የስራ ኃላፊዎች በበይነመረብ ባደረጉት ውይይት ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት በሀገሪቱ እምቅ የታዳሽ ሃይል የማምረት አቅም ቢኖርም የኢነርጂ አቅርቦቱ ከ50% በታች መሆኑን ገልፀው፤ የኢነርጂ አቅርቦቱን ለማሳደግና በቀጠናው የተጀመረውን የሀይል ትስስር ለማስፋፋት ኢነርጂ የማምረት፣ የማሰራጨትና የማስተላለፍ አቅም ማሳደግ አሰፈላጊነትን አመላክተዋል፡፡ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በበኩላቸው ከህዝብ ቁጥር መጨመርና የኢነርጂ ፍላጎት እያደገ መሄድ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ የኢነርጂ የማምረት አስፈላጊነትን አንስተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን አውስተዋል፡፡ የሩስሀይድሮ(RusHydro) የስራ ሀላፊዎች በበኩላቸው የዳበረ የሃይል ማምረት እና የማሰራጨት ልምድ እንዳላቸው ገልጸው፤ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሀይል ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውንና በኢትዮጵያም መሰማራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ በበይነመረብ ውይይቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የበላይ አመራሮች፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የስራ ሀላፊዎችና የሩስሀድሮ(RusHydro) የስራ ሀላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Share this Post