ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከአለም ባንክ የውሃ ዘርፍ ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር እና ልኡካን ቡድናቸው ጋር ተወያዩ፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚንስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከአለም ባንክ የውሃ ዘርፍ ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር እና ልኡካን ቡድናቸው ጋር ተወያዩ፡፡ መጋቢት /2015ዓ.ም የአለም ባንክ የውሃ ዘርፍ ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር እና ልኡካን ቡድናቸው በክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞን ጨምሮ ሌሎች የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የውሃ ዘርፍ ኃላፊዎች በተገኙበት በሀገር አቀፍ የውኃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ዘርፉ ያለበትን አሁናዊ ቁመናና የወደፊት ትልም በሚያሳይ መልኩ አጭር ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ በጽሑፉ እንደተገለጸው የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ወደ 1.3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ያበረከተ ሲሆን በዚህም እስከ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትየጵያውያን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲኖራቸው ለማድረግ ተችሏል፡፡ በቀረበው አጭር ጽሑፍ ላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በገጸ ምድርና ከርሰምድር ያላት የውሃ ሀብት ተብራርቶ የቀረበ ሲሆን የውሃውን ዘርፍ በማስተዳደር ሂደትም ከድርቅ፣ ጦርነት፣ ከጎርፍ አደጋ እና ከመሬት አቀማመጥ እንዲሁም ከማስፈጸም አቅም ውስንነት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች መኖራቸው ተብራርቷል፡፡ በውይይቱም ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉን ፖሊሲ ከመከለስና አዲስ ተቋማዊ መዋቅር ከማዘጋጀት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የውሃ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በግብዓት አቅርቦት ላይ የሚታየው የዓለም የገበያ ዋጋ ንረት፣ የግዥ ሂደት መጓተት፣ ከመፈጸም አቅም፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ፣ እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውስንነቶች ለውሃው ዘርፍ እንቅፋት እንደነበሩ ገልጸው በቀጣይ አቅም ግንባታው ላይ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ የአለም ባንክ የውሃ ዘርፍ ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር በኢትዮጵያ አሀዳዊ የዋሽ ፕሮግራምን ጨምሮ በዘርፉ ያለውን የብዝሀ ሴክተሮች የጋራ እንቅስቃሴ ከሚታየው ተጨባጭ እድገትና ተደራሽነት ጋር እንደሚያደንቁና ባንኩ ዘርፉ በሚፈልጋቸው እስትራቴጅያዊ የድጋፍ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ባንኩ በአጽኖት ከሚደግፋቸው ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደመሆኗ መጠን በልዮ ትኩረት እንደሚመለከቱትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡

Share this Post